የዓባይ ባንክ ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን አከበሩ Solomon Aynishet December 5, 2025

የዓባይ ባንክ ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን አከበሩ

1

የዓባይ ባንክ ሠራተኞች ዓለምአቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል በፓናል ውይይት አክብረዋል።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠ እንደተናገሩት፣ ሠራተኞች በሥነ-ምግባር ታንፀው ሙያዊ የሥራ ዲሲፒሊን በመላበስ የማገልገል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተው፣ የባንኩ ሠራተኞች የተቋማችንን እሴቶች፣ የስነምግባር መርሆዎች፣ የአገሪቱን ህጎችና የባንኩን አሠራር ፖሊሲዎች አክብረን በመሥራት የተቋሙን ዓላማ ማሳካትና ሙስናን መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

የባንኩ ሠራተኞች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የመልካም ሥነ-ምግባር እሴቶችን መሰረት በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአመርቂ ሁኔታ በመወጣት እና ብልሹ አሠራርን በጋራ በመከላከል መሆን እንዳለበትም አቶ የኋላ አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ጥራት ያለው እና ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎት በመስጠት፣ የተገልጋዩን ጊዜ እና ገንዘብ በመቆጠብ ባንኩ በማህበረሰቡ ዘንድ ያሰረጸውን ታማኝ አገልጋይነትን ይበልጥ በማጎልበት ሙስናን መከላከል እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የዓባይ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱን ሲያጠናቅቁ የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ በባንኩ ታማኝነትን እና ሐቀኝነትን በመገንባት ሙስናን ለመከላከል ቃል ገብተዋል፡፡

ባንኩ በቀጣይም ለመላው ሠራተኞቹ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ውይይቶች፣ ስልጠናዎች እና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት በሥነ-ምግባር የታነፁና ሙያዊ የሥራ ዲሲፕሊን የተላበሱ ሠራተኞን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡

22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን “ትውልድን በሥነምግባር፤ ተቋምን በአሠራር!” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ይገኛል፡፡

Write a comment
Your email address will not be published.