ዓባይ ባንክ ታሪካዊና ስኬታማ ትርፍ አስመዘገበ Mulualem Kebede November 17, 2025

ዓባይ ባንክ ታሪካዊና ስኬታማ ትርፍ አስመዘገበ

photo 2025 11 17 13 36 34

ዓባይ ባንክ ታሪካዊና ስኬታማ ትርፍ አስመዘገበ፣ዓባይ ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በማትረፍ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነ ስኬት ማስመዝገቡን በዛሬው ዕለት በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል በተካሄደው የባንኩ የባለአክስዮኖች 16ኛ መደበኛ እና 8ኛ አስቸኳይ ድንገተኛ ጉባዔ ላይ አስታውቋል፡፡

በጉባዔው ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አምላኩ አስረስ (ዶ/ር) የ2017 ታሪካዊና ሥኬታማ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባንኩ የ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ታሪካዊ ትርፍ በማስመዝገብ፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ116 በመቶ ጭማሪ እንዲሁም የጠቅላላ ገቢውን በ58 በመቶ ማሳደግ ችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከባለፈው ዓመት በ36 ነጥብ 7 በመቶ በማደግ 71 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የባንኩ የገንዘብ ጥንካሬ እና ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ የታየበት ሌላው ምዕራፍ፣ የተከፈለ ካፒታል በ17 በመቶ በማሳደግ 7 ቢሊዮን ብር ላይ መድረሱ ዓባይ ባንክ በአስተማማኝ ጥንካሬ የታላቅነት ጉዞውን ዕውን እያደረገ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

የደንበኞች መረጃ በማጥራት እና ትርፋማ የሆኑ ሒሳቦችን ብቻ በመያዝ በተደረገው ጠንካራ ሥራ፣ የደንበኞች ቁጥር ዕድገት 3 ነጥብ 6 ሚሊየን መድረሱን እንዲሁም ጠቅላላ የብድር እና የቅድሚያ ክፍያዎች ወደ 49 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መሻገሩንም ዶ/ር አምላኩ አክለው ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ማድረጉን ሰብሳቢው አስታውሰው፣ ይህም የሥርዓት አቅርቦት እና አፈጻጸምን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል ብለዋል። ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ ከጠቅላላ ግብይቶቹ 69 በመቶ የሚሆነው ግብይት የተከናወነው በዲጂታል አሠራር ሲሆን ይህም የእኛን የአገልግሎት አሰጣጥ እመርታ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።  

የባንኩ ቀጣይ ትኩረት አሁን የተመዘገበውን ታሪካዊ ስኬት ማስቀጠል ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የላቀ አገልግሎት መስጠትን በማስቀጠል፣ የሥራ ቅልጥፍናን እና ተቋማዊ ልዩነት ፈጣሪነትን የሚያጠናክሩ ስትራቴጂያዊ እቅዶችን በማስፈን የበለጠ ውጤት በማስመዝገብ ላይ እንደሚሆን አምላኩ አስረስ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር አምላኩ በተሰጣቸው ኃላፊነት ጠንክረው ለሚታትሩ እና ቁርጠኛ ለሆኑ የባንኩ ሠራተኞች፣ ደንበኞች ላሳዩት ተደጋጋሚ እምነት እና ድጋፍ፣ ባለአክሲዮኖች የባንኩ የዕድገት እቅድ እውን እንዲሆን ላሳዩት የማያቋርጥ ድጋፍ እና እምነት እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ፣ ቁርጠኛ እና ወሳኝ ለሆነው የማሻሻያ አጀንዳው እና ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠር እያደረገው ላለው ጥረት ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Write a comment
Your email address will not be published.