ዓባይ ባንክ በደሴ ከተማ ያስገነባውን የደሴ ዲስትሪክት ጽ/ቤት ዘመናዊ ሕንጻ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ የዓባይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የኋላ ገሠሠ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባንካችን በመላው ሀገሪቱ ከሚያስገነባቸው ግዙፍ ሕንጻዎች መካከል የመጀመሪያውን የዓባይ ባንክ ደሴ ዲስትሪክት ሕንጻ ግንባታን አጠናቅቀን በማስመረቃችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል ያሉት አቶ የኋላ አክለውም ሕንጻው ለውቧ ደሴ ከተማ ከሚጨምረው ሞገስ ባሻገር፣ ባንኩ የሚሰጣቸውን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ወደላቀ ከፍታ በማሸጋገር፣ ፈጣን ምላሽ በመስጠት እና በበለጠ ትጋት ለማገልገል አቅም ይጨምራል ብለዋል።
ከሐምሌ 7፣ 2017 ዓ.ም ጀምሮ 15ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ ለሚገኘው ዓባይ ባንክ የሕንጻው ምረቃ ተጨማሪ ድምቀት እንደሆነም አቶ የኋላ ተናግረዋል።
ዓባይ ባንክ የስትራክቸራል ግንባታዎች የተጠናቀቁበት ባለ 33 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ እና ባለ 14 ወለል ሕንጻ በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም ባለ 12 ወለል ሕንጻ በባህርዳር በማስገንባት ላይ ሲሆን፣ የእነዚህ ሕንጻዎች ግንባታ ባንኩ በሀገርአቀፍ ደረጃ ሁሉንአቀፍ በሆነ መልኩ እያስመዘገበ ያለውን ዕድገት ማሳያ መሆናቸውንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
አቶ የኋላ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳደር፣ የደሴ ከተማ ከንቲባ፣ የኮምቦልቻ ከተማ ከንቲባ፣ የደሴ መናፈሻ ክፍለ ከተማ አመራሮች፣ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች፣ ለሕንጻው ኮንትራክተር ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬት እና ለግንባታ አማካሪው ለልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን የሕንጻው ግንባታ መጠናቀቅ እውን እንዲሆን ላበረከቱት ዘርፈብዙ ድርሻ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
