ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም /ትምህርት ቢሮ/ ዓባይ ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እና የትምህርት ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ወላጆች እና ልጆች ከትምሕርት ገበታቸው እንዳይቀሩ የሚያግዝ የ50,000 ባለ50 ገጽ ደብተሮችን ለአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስረክቧል፡፡
ድጋፉ በክልሉ በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል እየፈለጉ በቁሳቁስ ዕጥረት ለተቸገሩ ተማሪዎች በፍትሐዊነት ለሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የሚሰራጭ ነው።
የትምሕርት ቁሳቁስ ድጋፉ በአማራ ክልል መማር እየፈለጉ በአቅም ማነስ እና በሌሎች ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት እገዛ ማግኘት ላልቻሉ ተማሪዋች በባንኩ መለያ በልዩ ህትመት የተዘጋጁ ደብተሮች ናቸው።
ርክክቡ ዛሬ ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ ሲካሄድ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ ባደረጉት ንግግር፣ “የክልሉን የትምሕርት ስትራቴጂ ከማሳካት አኳያ እንደ ዓባይ ባንክ ያሉ አጋሮች የተቀናጀ ኢንቨስትመንት ከማካሄድ ባሻገር የማኅበራዊ ልማት ላይ በንቃት መሳተፍ ድርሻው ከፍ ያለ ነው” ብለዋል።
ሀገራዊ የትምህርት ዘርፋን ለማሳደግ እና የተማሪዎችን ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን እንደ ዓባይ ባንክ ያሉ ቀዳሚ የልማት እና የፋይናንስ አጋሮች የሚያደርጉት ድጋፍ ለሌሎችም ምሣሌ የሚሆን ነው ተብሏል።
ኃላፊው በክልሉ የትምህርት ዘርፍ የመሠረተ-ልማት እና የግብዓት እጥረቶችን ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የፋይናንስ ተቋማት እገዛ ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፣ የዓባይ ባንክ የመማሪያ ደብተር ድጋፍም በከልሉ የተማሪዎችን የማቋረጥ ምጣኔን ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ዐቅም ይኖረዋል ብለዋል። ድጋፋ በትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ወደ ትምህርት ገበታ መሄድ ያልቻሉ የክልሉ ተማሪዋችን ችግር ለመቅረፍ እና “በዚህ ችግር ወደ ትምህርት ገበታቸው ያልመጡ ተማሪዋችን ተስፋ የሚያለመልም ነው” በማለት ምስጋናቸውን ለባንኩ አቅርበዋል፡፡
የዓባይ ባንክ ስትራቴጂ ዋና መኮንን አቶ ወንድይፍራው ታደሰ ባንኩ የማኅበራዊ ልማት ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ እያከናወነ ያለውን ድጋፍ አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ዓባይ ባንክ “በእያንዳንዱ የማኅበረሰብ ጎጆ ገብቶ ቀዳሚ የፋይናንስ አጋር የመሆን ፍኖት እና በቀጣዩ ትውልድ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ዕውቀት-መር የኢንቨስትመንት አስተሳሰብ መገንባት” እየተተገበረ ያለ አቅጣጫ መሆኑን አሳውቀዋል። ባንኩ በተለያዩ ዘርፍች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ እና የማህበራዊ ኃለፊነት የመወጣት ዕቅዱ አካል የሆኑ ድጋፎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚገኙ ተቋማት እና ዜጎች ሲያደርግ መቆየቱንም አውስተዋል።
ዓባይ ባንክ በፋይናንሱ ዘርፍ ለብዙዎች የታላቅነት ምንጭ ከመሆን ባሻገር የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትን እንደ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ የማኅበረሰብ አጋርነት እና ተቋማዊ ትሥሥር ዓላማ ያውለዋል፡፡
ዓባይ ባንክ አሁን ላይ ካደረገው የትምህርት ግብዓት ድጋፍ ባሻገር በጥቅል የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከ4.8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ደንበኞቹ ሰፊ የዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች በማቅረብ ግንባር ቀደም የፋይናንስ አጋር በመሆን እየሠራ ነው።




ዓባይ – የታላቅነት ምንጭ!