ዓባይ ባንክ ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ያዘጋጀው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ሥራ ጀመረ Solomon Aynishet April 24, 2026

ዓባይ ባንክ ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ያዘጋጀው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ሥራ ጀመረ

photo 2026 04 24 16 00 34

ዓባይ ባንክ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገንዘብ አስተዳደርን በማዘመን የደንበኞችን ውጣ ውረድ ማስቀረት የሚያስችል የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ 

በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የዓባይ ባንክ የሐብት ማሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ደመቀ እንደተናገሩት፣ ደንበኛ ተኮር ከሆነው የዘመናዊ ገንዘብ አስተዳደር ቴክኖሎጂ ማበልጸግ ጋር በተያያዘ የቤተ-ክርስቲያኗ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ይዞት የተነሳውን ግብ ዕውን ለማድረግ ዓባይ ባንክ እያከናወናቸው ያሉ ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ ተግባራት ተመራጭ አድርጎታል፡፡

በስምምነቱ ባንኩ ያቀረበው የቴክኖሎጂ አማራጭ ዘመኑን የዋጀ፣ በቀላል መንገድ ሊተገበር የሚችል፣ ደንበኞች ያለምንም ውጣ ውረድ ኪራያቸውን በሞባይል ባንኪንግ እንዲከፍሉ የሚያስችል፣ የመክፈያ ጊዜ ሲደርስ ማስታዎሻ መልዕክት የሚልክ፣ ከክፍያ በኋላ አመስግኖ የሚቀበል፣ ጊዜው ያለፈባቸውን ክፍያዎች ከነቅጣታቸው እንዲከፍሉ ማስታወስ የሚያስችል እንዲሁም የመሳሰሉትን የሚተገብር መሆኑም አቶ ማርቆስ አብራርተዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ደንበኞች ተጠቃሚ በመሆን ክፍያን ከፍለው ደረሰኝ ለማወራረድ የሚያባክኑትን ጊዜ መቆጠብ የሚያስችል መሆኑም ታውቋል፡፡

ይህ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አገልግሎት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።