ዓባይ ባንክ ከሁሉም ዲስትሪክቶች ለተውጣጡ ተተኪ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች የ4ኛ ዙር የፋይናንስ ኢንዱስትሪ አመራር ብቃት ማሳደጊያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የዓባይ ባንክ የሪቴል ባንኪንግ ዋና መኮንን አቶ አሰፋ ተፈራ ስልጠናው የባንኩን የወደፊት መሪዎች አስፈላጊ በሆኑ የአመራርና የቴክኒክ ክህሎቶች እንዲሁም ውጤታማ የአስተዳደር ልምዶችን በሚመለከት ግንዛቤ በማስጨበጥ አቅማቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።
አቶ አሰፋ አክለውም ዓባይ ባንክ በዓለም አቀፍ እና በአገራዊ የፋይናንስ ዘርፎች የሚታዩ የዕድገት ሂደቶችን ቀድሞ በመረዳት ብቁ መሪዎችን ለማፍራት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ባንኩ የሠራተኞችን አቅም በየጊዜው በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች የማብቃት ተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡
የዓባይ ባንክ የሰው ሐብት ዋና መኮንን አቶ በለጠ ቀኔ በበኩላቸው ሰልጣኞች በሙሉ ትጋት እና መንፈስ ሥልጠናውን በመከታተላቸው እና በማጠናቀቃቸው አመስግነው፣ ለባንኩ ሁሉንአቀፍ ዕድገትና ውጤታማነት በተግባር ላይ እንዲውል አሳስበዋል።
ኃላፊዎቹ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ያበለጸጉትን የዳበረ ልምድ ለሰልጣኞች ያካፈሉ ሲሆን፣ ከሰልጣኞች ለቀረቡ ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዓባይ ባንክ በሰው ሐብት ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ ግለሰቦችን ለወደፊት የኃላፊነት ሚናዎች ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ባንኩ በየደረጃው ባለው ጠንካራ አመራርና ዕውቀት ማጎልበትን ለማረጋገጥ በውስጥ አቅም ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት የሠራተኞችን የተተኪ መሪነት ብቃት፣ ዕውቀትና ክህሎት የማሳደግ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
ስልጠናው ከጥቅምት 2 – 13 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የተሰጠ ሲሆን፣ ስልጠናውን ላጠናቀቁ ሠራተኞች የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡




ዓባይ – የታላቅነት ምንጭ!